Wednesday, Dec 10, 2014
ዓይኖቼን ክፈት
ንጉሥ
ዳዊት
“ዓይኖቼን ክፈት ከሕግህም ተአምራትህን አያለሁ” (መዝሙር 119፡18) ብሎ የጸለየውን ጸሎት ባሰብኩት ቁጥር እጅግ ያስደንቀኛል፡፡ትልቅ ጸሎት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡አዎ መንፈስ ቅዱስ ዓይኖቻችንን ካልከፈተው በስተቀር፣መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት መረዳት ይከብዳል፡፡ለዚህ ነው በጸጋው ዙፋን ፊት በቂ ጊዜ በጸሎት ማሳለፍ የሚገባን፤ለዚህ ነው የመንፈስ ቅዱስ ርዳታ ያለማቋረጥ የሚያስፈልገን፡፡በግሌ እግዚአብሔር ዓይኖቻችንን እንዲያበራልን መማጸኑ፣መጮኹና ነፍስን ወደ ላይ ማንሳቱ ጥበብ ነው ብዬ አስባለሁ፤“ማስተዋልን
ወዳጄ ብለህ ጥራት” (ምሳሌ 7፡4)ተብሎ ተጽፎልንስ የለ?
ንጉሥ
ዳዊት
“የእግዚአብሔር ትእዛዝ ብሩህ ነው፥ ዓይንንም ያበራል” (መዝሙር 19፡8) ብሎ ተናግሯል፡፡እውነት ነው፡፡የእግዚአብሔር ቃል
በመንፈስ ቅዱስ ታግዘን ሲፈታ፣ዓይናችንን ይከፍተዋል፣ቀድሞ አንበበነው ያለፍነውን ምንባብ ማስተዋልም እንድንችል ያደርገናል፡፡ነገር
ግን የጌታ መንፈስ ካልረዳንና ፍቺውን ካልገለጠልን፣እውቀታችን ውሱንና ግልብ ነው የሚሆነው፡፡አዎ!መንፈሳዊውን
ዓለም
ለማስተዋል፣የእግዚአብሔር መንፈስ እገዛ እጅግ ያስፈልገናል፡፡አለበለዚያ አንድ ርምጃ መሄድ አይቻልም፡፡የፈለገውን ያህል ብሩህ አእምሮ ያለን ሰዎች ብንሆን፣የሚያምን ትሑት ልብ ከሌለንና በጌታ መንፈስ ላይ ካልተደገፍን፣ከሐሳቡ ጋር እንተላለፋለን፣ሐሳቡን እንስታለን፡፡እርግጥ
መረጃ ጥሩ ነው፤የቀለም ዕውቀት ጥሩ ነው፤ነገር ግን አሁን ዋና የሚያስፈልገን ጉዳይ የልብ ብርሃን(በኢንግሊዝኛው ኢንሳይት)ነው፤የሚያስፈልገን መገለጥ ነው፤የሚያስፈልገን በማስተዋል የሚገኝ መረዳት ነው፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በክርስቶስ ያገኙትን ማንነትና በረከት ከኤፌሶን 1፡1-11 ድረስ አበክሮ ያስረዳቸዋል፡፡ከዚያም ይህንን ዕምቅ ሀብትና ሰማያዊ ብልጽግና በሚገባ እንዲያዩት ዓይኖቻቸው ይበሩ ዘንድ፣የጥበብና የመገለጥ መንፈስ እንዲሰጣቸው እንደሚጸልይ ነግሯቸዋል፡፡እንዲህ ብሎ ነበር የጸለየላቸው፡-
“የክብር
አባት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን በማወቅ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እለምናለሁ። ይህም የልባችሁ ዓይኖች ሲበሩ የመጥራቱ ተስፋ ምን እንዲሆን በቅዱሳንም ዘንድ ያለው የርስት ክብር ባለ ጠግነት ምን እንዲሆን ለምናምን ከሁሉ የሚበልጥ የኃይሉ ታላቅነት ምን እንዲሆን ታውቁ ዘንድ ነው” (ኤፌሶን
1፡17-19)
ይህንን የጸሎት ሐሳብ ዘርዘር አድርጌ እንድጽፈው ይፈቀድልኝ፡፡እንዲህ ነበር ያላቸው፡-
ከሱ
ጋር
በሚኖራችሁ የጠበቀ ጸሎትና የቃል ሕብረት(እርሱን በማወቅ)፣የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ ታገኛላችሁ፡፡የጥበብና የመገለጥ መንፈስ ስታገኙና ሲበዛላችሁ፣ዓይኖቻችሁ ይበራሉ፤ዓይኖቻችሁ ይከፈታሉ፡፡ዓይኖቻችሁ ሲበሩና ሲከፈቱ ደግሞ :-
- ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን እንደጠራችሁ ይገባችኋል
- በቅዱሳን ዘንድ ያለውን የርስት ክብር ባለጠግነት ትረዳላችሁ
- ኢየሱስን ከሞት ያስነሣውን የኃይሉን ታላቅነት ታውቃላችሁ
እጅግ
የሚደንቅና በክርስትና ሕይወታችን ሊጸለይ የሚገባ ጸሎት! ዓይን ሲበራ ደግሞ የሚሆነው ደግሞ አስደናቂ ነው፤ቃሉ “የዓይን ብርሃን ልብን ደስ ያሰኛል” (ምሳሌ 15፡30)ይላልና፡፡አዎ ቃሉ ሲበራና የጌታችን ኢየሱስ ጌትነቱ፣አዳኝነቱ፣ሁሉን ቻይነቱ ሲበራልን፣የመጀመሪያው የሚያገኘን በረከት አእምሮን የሚያልፍ ደስታ ነው፡፡የምናገኘውን ሐሤትና ደስታ ደግሞ ማንኛውም ምድራዊ ቋንቋ ሊገልጸው አይችልም፤አእምሮን ያልፋልና፣ልዩ ነውና፣ሰማያዊ ነውና፣መለኮታዊ ነውና፣ከላይ ነውና!እርሱ ብቻ አይደለም ፣ዓይኖቻችን ሲበሩ ጌታ ኢየሱስን ስናውቀውና ስንረዳው ከሱ ጋር ያለን ሕብረታችን ያድጋል፣ይጠልቃል፡፡የሕይወት ምልልሳችን እየተለወጠና እየጠነከረ ይሄዳል፡፡ይህ ለውጥ በዙሪያችን ያሉ እኛን የሚመለከቱ ሰዎችን ልብ ስለሚነካ ለውጡ ቀላል አይሆንም፣ፍሬውም እንዲሁ!
አባት
ሆይ
እናይህ ዘንድ ዓይኖቻችንን ክፈትልን!
በቀለ
ብርሃኑ(ዶ/ር)
beke_abay@yahoo.com
240-330-5004